የከተማ አስተዳደሩና ሪል ስቴት አልሚዎች ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ወጪ መኖሪያ ቤቶችን ሊገነቡ ነው

የከተማ አስተዳደሩና ሪል ስቴት አልሚዎች ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ወጪ መኖሪያ ቤቶችን ሊገነቡ ነው።

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግሥትና በግል አጋርነት ፕሮጀክት አማካይነት በመረጣቸው ሪል ስቴት አልሚዎች፣ ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ ወጪ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሊካሄድነው ተብሏል።

በዚህ ፕሮግራም ሥር እንዲሳተፉ 68 ሪል ስቴት አልሚዎችን የመረጠ ሲሆን፣ አልሚዎቹም በተቀመጠው 70/30 አጋርነት መሠረት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ተጣምረው ግንባታውን ለማካሄድ ውል ገብተዋል። 

ከእነዚህ ውስጥ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ ኦቪድ ግሩፕ፣ ፍሊንትስቶን ሆምስ፣ እንይ ኮንስትራክሽን፣ ጊፍት ሪል ስቴትና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የቤቶቹን ግንባታ ለማካሄድ የሚያስፈልገውን መሬት ከሊዝ ነፃ ማቅረብና መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ኃላፊገት ሲኖርበት አልሚዎቹ ደግሞ ያስገቡትን የመገንባት አቅም መሠረት ተደርጎ በሚቀርብላቸው መሬት ላይ ወጪውን በመሸፈን ቤቶቹን ይገነባሉ።

አልሚዎቹ የቤቶችን ግንባታ አካሂደው ካጠናቀቁ በኋላ፣ 30 በመቶውን ለከተማ አስተዳደሩ ለማስረከብ መስማማታቸው ታውቋል። በዚህም የከተማ አስተዳደሩ በ2016 በጀት ዓመት 100ሺ ቤቶችን ለማስገባት ማቀዱ ተጠቁሟል።

ከዚህ ውስጥ አቪድ ግሩፕ ተቋራጭ 60 ሺሕ ቤቶችን፤ ጊፍት ሪል ስቴት 12 ሺሕ ቤቶችን፤ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ 10 ሺሕ ቤቶችን ለመግንባት ውል መግባታቸውን ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

ለቤቶቹ ግንባታ የተለዩ ሦስት አካባቢዎች የተመደቡ ሲሆን እነሱም በከተማ ውስጥ፣ በከተማ አቅራቢያና ከከተማ ወጣ ያሉ ናቸው። የከተማ አስተዳደሩ በመንግሥትና በግል አጋርነት ለሚካሄደው የቤት ግንባታ ፕሮጀክት፣ በመሀል አዲስ አበባ 350 ሔክታር መሬት ማዘጋጀቱ ተገልጿል።

ለኩባንያዎቹ መሬቱ ከሊዝ ክፍያ ነፃ የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ከሚገነቧቸው ቤቶች 70 በመቶውን ለግላቸው ወስደው 30 በመቶውን ለመንግሥት ያስረክባሉ፡፡ ይህ ማለት የከተማ አስተዳደሩ በዚህ ጥምረት ከሚገነቡት ቤቶች ውስጥ 30 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል።

የፕሮጀክቱ ፋይናንስ ሙሉ በሙሉ የሚሸፈነው በአልሚው ድርጅት ሲሆን የግብዓት አቅርቦት፣ የመብራትና የውኃ፣ እንዲሁም ለግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እጥረት ሲፈጠር አልሚ ድርጅቶቹ ቅድሚያ እንዲያገኙ የማድረግ ኃላፊነት የከተማ አስተዳደሩ መሆኑም ታውቋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *